The FOM Newsletter masthead

ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ፤ በአዚናራ የብርታት ተምሳሌት

አርበኛ፣ መምህርት፣ የሕዝብ ተወካይ፣ ደራሲ እና የሴቶች መብት ተሟጋች

ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ

ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ

በኢትዮጵያ ታሪክ ቀደምት ከሚባሉት ዘርፈ ብዙ ባለሙያ የሕዝባቸው አገልጋይ የነበሩት ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ አርበኛ፣ መምህርት፣ በፓርላማ የሕዝብ ተወካይ፣ የሴቶች መብት ተሟጋች ነበሩ። ወይዘሮ ስንዱ በ1908ዓ.ም. ተወልደው፣ በአውሮፓ ለመማር ዕድል ካገኙት ጥቂት ኢትዮጵያውያን ሴቶች መካከል አንዷ ሲሆኑ፣ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ያላቸውን የታሪክ እውቀትና የሥነ ጽሑፍ ፍቅር በመጠቀም አገራቸውን በፅናት ሲያገለግሉ ኖረዋል።

ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ የጥቁር አንበሳን የጦር ድርጅት መሥራች አባል ሲሆኑ፣ የመጀመሪያዋ እንስት አባል ሆነው አገልግለዋል። በኋላም ጫናው ሲበዛ ራስ እምሩ ኃይለሥላሴ ወይዘሮ ስንዱን ከሃገር እንዲወጡ ሊያሳምኗቸው ቢሞክሩም፣ ወይዘሮ ስንዱ አሻፈረኝ በማለት ጥቁር አንበሳ ሲመሠረት አባላቱ የገቡት ቃለ መሓላ አገር ጥሎ መውጣት እስከ ሞት ድረስ ቅጣት እንደሚያስከትልና እርሳቸውም እዚያው ለመቆየት እንደወሰኑ ገልፀውላቸው፣ እንደውም ራስ እምሩ ቢፈቅዱና ድጋፍ ቢሰጧቸው የቀይ መስቀል ክንፍ መሥርተው ለጦሩ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ እንደሆኑ ባሳመኗቸው መሠረት እዚያው ቆይተው ቀይ መስቀልን መሥርተው አገልግለዋል።

ግራዚያኒን ለመግደል የተደረገው ሙከራ ከከሸፈ በኋላ ሁለት ዕድሜአቸው ሃያ አንድ ዓመት ያልሞላ ደበበና ኃይሉ የተባሉ የወንድማቸው ልጆች፣ ታናሽ ወንድማቸው መሸሻና ሌሎችም ብዙ የጥቁር አንበሳ አባላት በተገኙበት ተገድለዋል። ወይዘሮ ስንዱና በርካታ የቤተሰባቸው አባላት ታፍሰው ወደአዚናራ ተወሰዱ። በዚያ የነበረው የኑሮው ሁኔታ በጣም ከባድ፣ ብቸኝነቱና ከሰው መነጠሉም እጅግ አስከፊ ቢሆንም ወይዘሮ ስንዱ በብርታታቸው ተወጥተውታል።

በሚገባቸው ቋንቋ ሁሉ መጻሕፍት ማግኘት ባለመቻላቸው ወይዘሮ ስንዱ በራሳቸው ትጋት ጣልያንኛ መናገርና ማንበብ ተለማምደው፣ ያጋጠማቸውን እንቅፋት ወደ ዕድል የለወጡ ሰው ናቸው። አብረዋቸው ለታሰሩ ሰዎች መብት በመቆም፣ በተለየ ሴቶቹ እስረኞች አያያዛቸው እንዲሻሻል ትልቅ አስተዋጽዖ አድርገዋል። እኅት ወንድሞቻቸውንም በመጠበቅ በተለይ እኅታቸው ደስታ ገብሩን ጠፍተው አዚናራ ደሴት ወደሚገኝ ገዳም እንዳይገቡ ታድገዋቸዋል።

አዚናራ ደሴት ላይ በነበሩበት ጊዜ ወይዘሮ ስንዱ አብረዋቸው ከታሰሩ ሰዎች ጋር የዕድሜ ልክ ወዳጅነት መሥርተው ለአገራቸው ያላቸውን ተዓማኒነትና ለነፃነት ያላቸውን ጥማት ሲጋሩ ኖረዋል። የጥቁር አንበሳ መሥራች አባልነት ተሞክሮአቸውና የአዚናራ እስረኝነታቸውን አቀናጅተው "የልቤ መፅሐፍ" የተሰኘ የጣልያን ወረራና የኢትዮጵያውያንን አርበኝነትን የሚዘግብ ታሪካዊ ድራማ ደርሰዋል።

ጥቁር አንበሳ ውስጥና አዚናራ ላይ ያሳለፉት ጊዜ በኋላ አገርን ለማገልገል ሰፊ መሠረት ጥሎላቸዋል። ወይዘሮ ስንዱ ከነበሯቸው እጅግ ብዙ ኃላፊነቶች አንዳንዱን ለማንሣት ያህል፣ የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ዳይሬክተር፣ የፓርላማ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የቀይ መስቀል ኃላፊ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች በጎ አድራጎት ማኅበር አመራር፣ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ማሕበር አመራር በመሆን አገልግለዋል።

በኋላም ወይዘሮ ስንዱ በ1940ዎቹ ውስጥ ሻለቃ ለማ አሰፋን (በኋላ አምባሳደር) አግብተው የአራት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ አገራቸውን እና ሕዝባቸውን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። በ2001 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ድካም በ94 ዓመት ዕድሜአቸው እስካረፉበት ጊዜ ድረስና ከዚያም በኋላ ስማቸው የትጋት፣ የፅናትና የሕዝብ አገልግሎት ተምሳሌት ሆኖ ይኖራል።

ወይዘሮ ስንዱ አዚናራ በእስረኝነት የነበሩበት ዘመን ያጋጠማቸውን ተግዳሮት የተወጡበት መንገድ ሁሉ የሰው ልጅ ፈተናን ተቋቁሞ የራሱንም ሆነ የወገኑን ሕይወት ለማስቀጠል ላለው አቅም ምስክርነት የሚቆም ነበር። እሳቸው ራሳቸው እስረኛ ሆነው ሳለ ቤተሰባቸውን ጨምሮ ሌሎች እስረኞችን ለመታደግ የነበራቸው አቅም ከነፃነት በኋላ አገራቸውን በብቃት ለማገልገል እንደረዳቸው ጥርጥር የለውም።