
በ1910 አጋማሽ፣ በዘመነ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ፣ መርካቶ አካባቢ አንድ የድንጋይ ሕንጻ ተገነባ። ሕንጻው የተገነባው በወቅቱ የጦር ሚኒስትር ለነበሩት ለፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ መኖርያ እንዲኾን ታስቦ ነው። የጦር ሚኒስትሩ ወደዚኽ መኖርያ ቤት ከመዘዋወራቸው በፊት አሁን የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን የቆመበት ስፍራ[i] ላይ የተሠራ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር። የእርሳቸው አጃቢዎችም እዚያው አካባቢ ይኖሩ ስለነበረ መርካቶ ዙሪያ ሰፊ መሬትና ንብረት ነበራቸው። በርግጥ ያ በድንጋይ የተሠራና ግርማ ሞገስ ያለው ሕንጻ መኖሪያ ቤታቸው ብቻ ሳይኾን፤ ችሎት ማስቻያቸውም ነው።
ሕንጻው ከተገነባ ከኹለት ዐሠርት ዓመታት በኋላ ከወርኅ መስከረም ከ1928 ጀምሮ እስከ ጣሊያን ወረራ ፍጻሜ ድረስ፤ “በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር” በቀደሞው አጠራሩ “በኢትዮጵያ ነዋሪ የአሜሪካ ሚኒስትር” የነበሩት የኮርኔሊየስ ቫን ኤንግርት[ii] መኖርያ ቤት እና ፤ የአሜሪካን ቆንስላ ጽሕፈት ቤት በመኾን አገልግሏል። ይኽ ሕንጻ የአሜሪካን አምባሳደር መኖሪያ እና የአሜሪካን ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ኾኖ በማገልገሉ የተነሳ “አሜሪካን ግቢ” የሚል ተለምዷዊ ስያሜ አገኘ። ይኽ ስያሜ የአካባቢውም መጠሪያ በመኾን እስካኹን ድረስ እያገለገለ ይገኛል።

በየካቲት 12 ቀን 1929፤ ፋሺስት ጣሊያን “የጣሊያን ምሥራቅ አፍሪካ” ብላ ለሰየመችው ግዛት እንደራሴ የነበረው ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ ላይ የተደረገውን የግድያ ሙከራ ተከትሎ፤ በዐዲስ አበባ ውስጥ ለሦስት ቀናት የቆየ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ተካሄደ።[iii] በዚህ ወቅት “ጥቁር ሸሚዝ” (Black Shirts) በመባል የሚታወቁት የፋሺስት ጣሊያን ሚሊሻዎች፣ መደበኛ ወታደሮች እና ካራቢኔሬ (ፖሊሶች) በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በአሰቃቂ ኹኔታ ጨፈጨፉ።[iv]
በነዚያ የጭንቅ ቀናት፤ በአሜሪካን ግቢ አቅራቢያ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ለማትረፍ ወደ “አሜሪካን ግቢ” (የአሜሪካን አምባሳደር መኖሪያ እና የአሜሪካን ቆንስላ ጽሕፈት ቤት) ሸሹ። አምባሳደር ኮርኔሊየስ ኤንግርትም ኹለቴ ማሰብ ሳያስፈልጋቸው ሕይወታቸውን ለማትረፍ የመጡትን ኢትዮጵያውያን አስጠልለዋቸዋል። በወቅቱ በተደረገው ቆጠራ መሠረት፣ ከየካቲት 12 እስከ 16 ባሉት ቀናት ውስጥ ወደ 700 ኢትዮጵያውያን በ“አሜሪካን ግቢ” ውስጥ ተጠልለው ነበር። ከእነዚኽም መካከል 248 ወንዶች፣ 262 ሴቶች እና 195 ሕፃናት ነበሩ።[v]
የአምባሳደሩ ጠንካራ አቋም

የካቲት 16 ቀን 1929 የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስተር ለኤንግርት በላኩት የቴሌግራም መልዕክት፤ መሥሪያ ቤቱ በአካባቢው ለነበሩ ኢትዮጵያውያን መጠለያ መስጠቱን ከሰብኣዊነት አንጻር መቀበሉን፤ ነገር ግን የኢትዮጵያውያኑ እዚያ መገኘት በአምባሳደሩ እና በሠራተኞቻቸው ላይ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል፤ በዚያ የተጠለሉት ኢትዮጵያዊያንን ሕይወት ለአደጋ በማያጋልጥ መልኩ ከግቢው ለማስወጣት ዝግጅት እንዲያደርጉ መከሯቸው።[vi] አምባሳደር ኤንግርት ግን በግቢው ለተጠለሉት ኢትዮጵያዊያን ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት፤ ከጣሊያን ባለሥልጣናት ዋስትና ሳያገኙ ኢትዮጵያዊያኑን ከግቢው ማስወጣት አልፈቀዱም።[vii]
እነዚያ በሕንፃው ውስጥ ተጠልለው ሞትን ያመለጡ ኢትዮጵያዊያን መውጣት የጀመሩት፤ ኤንግርት ከጣሊያን ባለሥልጣናት ዋስትና ካገኙ በኋላ ነበር። ጭፍጨፋው ከተጀመረ ከስድስት ቀናት በኋላ በየካቲት 19 ቀን ኢትዮጵያውያኑ ግቢውን ለቅቀው ወጡ።[viii] ግቢውን ለቅቀው ከወጡ በኋላ የሰዎቹን ዕጣ ፈንታ በሚመለከት፤ የአሜሪካው አምባሳደር ለውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም ቢሉም፤ የእንግሊዝ ፓርላማ አባል የዓይን እማኞችን ቃል መሠረት በማድረግ ከግቢው ሲወጡ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ለፓርላማው ሪፖርት እንዳደረጉ ኢያን ካምፕቤል በመጽሐፉ ገልጿል።[ix]
“አሜሪካን ግቢ” ከነፃነት በኋላ በኢትዮጵያ ለሚኖሩ የየመን ማኅበረ ሰብ አባላት እንደ ትምህርት ቤት ሆኖ እንዲያገለግል ተሰጥቷል። የመናውያኑም ከ70 ዓመታት በላይ ሲገለገሉበት ቆይተዋል። ታሪክ የሚያስበው ይገኝ እንጂ ተዳፍኖ አይቀርምና ከጭፍጨፋው 84 ዓመታት በኋላ፣ እ.ኤ.አ. በ2021 በዐዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካን ኤምባሲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል፤ ታሪካዊ ሕንጻዎች እንዳይፈርሱና ተጠብቀው እንዲቆዩ በመሟገት የሚታወቀውን፣ “ሄሪቴጅ ዎች ኢትዮጵያ” የተሰኘ ሀገር በቀል ድርጅትን በመቅጠር፤ በግቢው ውስጥ ተጠልለው የነበሩ ሰባት መቶ ሰዎች መጨረሻ ምን እንደኾነ እንዲያጠናለትና፤ ከተገኙም የልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸው ምስክርነት እንዲሰንድለት ይጠይቃል።[x]
የተረፉትን ፍለጋ


ከጭፍጨፋው የተረፉትን ኢትዮጵያውያን፤ ቤተ ሰቦች፣ ልጆች እና የልጅ ልጆች ለማግኘት የተደረገው ጥረት ከመጀመሪያው ጀምሮ ፈታኝ ነበር። ኾኖም ጉዳዩን የያዙት ሰዎች እንደ ሰንበቴ ማኅበር ባሉ ሃይማኖታዊ አደረጃጀቶች ላይ ትኩረት በማድረጋቸው የማታ ማታ ለውጤት አብቅቷቸዋል። በአንዱ ሰንበቴ ማኅበር አማካኝነት ቡድኑ የመጀመሪያ የመረጃ ምንጩ የኾኑትን አቶ ምትኩ ገብረሚካኤልን አገኘ። እርሳቸውም የተጠቆሙት በእኅታቸው በወይዘሮ ሳካምየለሽ ገብረሚካኤል በኩል ሲኾን አባታቸው በደብረ አሚን ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው የታላቁ የሰንበቴ ማኅበር መሥራች ሲኾኑ እርሳቸውም አባታቸውን ተክተው የሰንበቴው አባል ናቸው።
አቶ ምትኩ ወላጆቻቸው በ“አሜሪካን ግቢ” አቅራቢያ ይኖሩ የነበሩ ሦስት ግለ ሰቦችን ስም አስታውሰው ከእነአድራሻቸው ለአጥኚው ቡድን ሰጡ። ቡድኑም ከተጠቆሙት ሰዎች መካከል አቶ ታዬ የተባሉትን ሰው ሲያናግር፤ አባታቸው አቶ ገብረሚካኤል ገብርዬ እና እናታቸው ወይዘሮ ዓለሚቱ ገብሩ በቆንስላው ጽሕፈት ቤት ውስጥ ተጠልለው ሕይወታቸውን እንዳተረፉ አረጋገጡ። ስማቸውም በግቢው ውስጥ በተጠለሉ ሰዎች ስም ዝርዝር ተራ ቁጥር 99 ላይ ተገኘ። በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ በተራ ቁጥር 100 ላይ ተመዝግበው የሚገኙትን የአቶ ተገኝ እምሩ እና የባለቤታቸው የወይዘሮ ወሰኔ አቦዬን ልጅ እና የልጅ ልጆች ማግኘት ቻሉ።[xi]
የካቲት 15 ቀን 2014 የአሜሪካን ኤምባሲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል በግቢው ውስጥ ልዩ የሕዝብ መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በመድረኩ ላይ ታዋቂው አርክቴክት ፋሲል ጊዮርጊስ የሕንጻውን ታሪክ፣ ኢያን ካምቤል የኤንግርትን ጀግንነት፣ እና “የሄሪቴጅ ዎች ኢትዮጵያ” ዳይሬክተር ልዕልት አስቴር አንቶሒን ደግሞ የምርምር ውጤቱን አቅርበዋል። በዕለቱም ከ85 ዓመታት በፊት የወላጆቻቸው ሕይወት በተረፉበት በዚያው ሕንጻ ውስጥ ከጭፍጨፋው የተረፉት ኢትዮጵያውያን ልጆች እና የልጅ ልጆች እንዲገኙ ተደርጓል።[xii]

ማጣቀሻዎች
[i] ይህ መረጃ የተገኘው ለሁለት ዓመት ተኩል ሕንፃውን አድሶ የማቆየት ኃላፈነት ወስደው ከሠሩት ፍቅረሥላሴ ስፍር ከተባሉት ታሪካዊ ቦታዎችን በማስጠበቅ ከሚታወቁት አርኪቴክት ነው።
[ii] The Saved 700. (2023, July). State Magazine. https://statemag.state.gov/2023/07/0723feat04/
[iii] እንግሊዛዊው የታሪክ ተመራማሪ ኢያን ካምቤል፤ የየካቲት ዐሥራ ኹለቱን አሰቃቂ ጭፍጨፋ. የተመለከቱ አራት የተዋጣላቸው መጻሕፍትን አሳትመዋል። እነዚህም መጻሕፍት፤ "The Plot to Kill Graziani" (2010) (የግድያውን ሙከራ ሙሉ ታሪክ የሚተነትን) ፤ "The Massacre of Debre Libanos" (2014) (በሺዎች የሚቆጠሩ መነኰሳት፣ ቀሳውስት እና ዲያቆናት የተረሸኑበትን ኹኔታ በዝርዝር የሚያብራራ) ፤ "The Addis Ababa Massacre" (2017) (በመዲናዋ ለሦስት ቀናት የተካሄደውን የንጹሐን ዜጎች ጭፍጨፋ የሚተነትን) እና "Holy War" (2021) (በጣሊያን ወረራ ወቅት የቫቲካንን ዐቋም ምን እንደነበር የሚያሳይ) ይሰኛሉ።
[iv] አምባሳደር እምሩ ዘለቀ ሰኔ 24 ቀን 2014 ከሄሪቴጅ ዎች ኢትዮጵያ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ያንን ዘግናኝ የጭፍጨፋ ወቅት ኣስታውሰዋል። ፋሺስት ጣሊያኖች ዕድሜም ኾነ ጾታ ሳይለዩ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ለመግደል ጠብመንጃ፣ ሳንጃ፣ ቢላዋ፣ አልፎ ተርፎም ዶማና አካፋ ሲጠቀሙ በዐይናቸው መመልከታቸውን አምባሳደሩ ተናግረዋል። በተጨማሪም እ.ኤ.አ. በ2016 በታተመው “A Journey: Memoirs” በሚለው የግል ማስታወሻቸው ገጽ 29 ላይ ይህንኑ ሐሳብ አስፍረዋል።
[v] U.S. Department of State. (1954). Foreign relations of the United States, 1937 (Vol. 2). p. 682 & 684
[vi] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 686
[vii] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 682
[viii] ዝኒ ከማሁ፣ ገፅ 684
[ix] Campbell, Ian. (2017). The Addis Ababa massacre: Italy’s national shame. Oxford University Press. p. 235.
[x] The Saved 700. (2023, July). State Magazine. https://statemag.state.gov/2023/07/0723feat04/
[xi] Heritage Watch Ethiopia. (2023). Revisiting narratives of Yekatit 12, 1937
[xii] The Saved 700. (2023, July). State Magazine. https://statemag.state.gov/2023/07/0723feat04/
ምንጮች
Ian Campbell. (2017). The Addis Ababa massacre: Italy’s national shame. Oxford University Press.
Imru Zelleke (2016). A journey: Memoirs. CreateSpace Independent Publishing Platform.
Heritage Watch Ethiopia. (2023, March 20). Revisiting narratives of Yekatit 12, 1937: In search of survivors at the American Gibbi (Unpublished report).
U.S. Department of State. (2023, July). Saved 700: Remembering a heroic act in Addis Ababa. State Magazine. https://statemag.state.gov/2023/07/0723feat04/
U.S. Department of State. (1954). Foreign relations of the United States diplomatic papers, 1937: The British Commonwealth, Europe, Near East and Africa (Vol. 2). U.S. Government Printing Office.