FROM OBLIVION TO MEMORYThe FOM NewsletterCommemorating Ethiopian prisoners of the Italo-Ethiopian Warቅጽ 1 · ቁጥር 2መስከረም/ጥቅምትfromobliviontomemory.org

ከዝግጅት ክፍላችን

የዘንድሮው የአሜሪካው የጣልያን ጥናቶች ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤውን ያካሄደው ከግንቦት 26 እስከ 28 ድረስ ሳሳሪ በምትባል የሳርዲኒያ(ጣልያን) ከተማ ውስጥ ነው። መዘክር ከሰሜን አሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የጣልያን ጥናት ክፍሎች የተውጣጡ ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ አስተማሪዎች እና ተማሪዎች በተገኙበት በዚኽ የሦስት ቀናት ጥናታዊ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ ንግግር እንዲያደርግ ተጋብዞ ነበር። በዚኽም መሠረት የመዘክር አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በስብሰባው ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። አለመረጋጋት፣ እንክብካቤ እና ነፃነት ጉባኤው ያተኰረባቸው ሦስት ጭብጦች መዘክርም ትኲረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። በተለይ አለመረጋጋት፤ ቁስን ወይም ሥነ ልቡናን የሚነካ፣ የደህንነት መጥፋትን ወይም አስተማማኝነት ማጣትን የሚመለከት እንደመኾኑ መጠን፤ ከቤታቸው ከሀገራቸው በግድ ሩቅ ተወስደው የታሠሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን ከገጠማቸው እና ካለፉበት ኹኔታ ጋራ በእጅጉ ይመሳሰላል። በሚያሳዝን መልኩ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን ኹኔታ በሚመለከት ያለው መረጃ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በጣልያኑ ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በአያትና ቅድመ አያቶቻችን ላይ የደረሰውን መከራ፣ በብቸኝነትና በስደት ያሳለፉትን ጊዜ እንዲኹም ትተዋቸው ስለሄዱት ልጆች እና ሌሎችም ሕይወት ለመረዳት ስለምናደርገው ጥረት እና ስለምንሠራው ሥራ ለማስረዳት ችለናል።

በግንቦቱ ጉባኤ የነበረን ሌላኛው መርሐ ግብር፤ የዛሬ ዓመት በመጀመሪያው የአዚናራ ጉዟችን ወቅት አግኝተናቸው የነበሩትን ጣልያናዊ አጋሮቻችንንና ሌሎችንም በማግኘት፤ ስለ ሥራችን ወቅታዊ መረጃዎችን ማካፈል ነበረ፡፡ በዚህም መሠረት ከአዚናራ ብሔራዊ ፓርክ አስተዳደር፣ ከሲላንድ አዚናራ አከባቢ የታሪካዊ አስጎብኚ ድርጅት፣ ከስቲንቲኖ ከንቲባ፣ ከሳሳሪ ከተማ ምክር ቤት ተወካይ እና ከሌሎችም ጋር ሰፊ ውይይት አካሄደናል፡፡ በውይይታችንም፤ ባለፈው ዓመት ካደረግነው የመጀመሪያው የአዚናራ ጉብኝታችን በኋላ በነበረው ጊዜ ውስጥ ስለ ሠራናቸው ሥራዎች፤ ማለትም፤ ሕጋዊ ዕውቅና ያለው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት መመሥረታችንን፣ ስለእያንዳንዱ እስረኛ መረጃ የመዘገብ እና የሕይወት ገጽታን በትክክል ማሳየት የሚችል ድንቅ ድረ ገጽ መሥራታችንን፣ በሦስት የተለያዩ ቋንቋዎች የሚቀርቡ አራት በደንብ የተጠኑ የዜና መጽሔቶችን ማዘጋጀታችንን በመግለፅ ምን ያህል የመሥራት አቅም እንዳለን ማሳየት ችለናል። አጋሮቻችንም፤ እስካሁን ያለውን ተግባርና ጥረት ባግባቡ ተረድተው ሥራችንን በመደገፍ እ.ኤ.አ. በ1937 አዚናራ ውስጥ ታስረው ለነበሩት ኢትዮጵያውያን ቋሚ መታሰቢያ ሊቆምላቸው የሚችልበትን መድረክና ኹኔታ ለማመቻቸት ቃል ገብተውልን ተሰነባብተናል።

የመዘክር አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በዚህ አጋጣሚ፤ ለልጅ ኃይሌ ወልደ መስቀል በተዘጋጀ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ የመገኘት ዕድል አግኝተዋል። ልጅ ኃይሌ ወልደ መስቀል የኤልፊ ኑቬሎን ቅድም አያት ሲኾኑ ታስረው የነበረው፣ ሕይወታቸው ያለፈውና ቀብራቸው የተፈጸመው ጣልያን ሳሳሪ ውስጥ ነው። የልጅ ኃይሌ መታሰቢያ እንዲመረቅ የተደረገው በኢጣልያ ወረራ ወቅት የተጠቃን አንድ ቤተሰብ ለመዘከር ታስቦ ሲኾን ሥነ ሥርዓቱም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህን ፀሎት የተመራና የአካባቢው የኢጣልያ ባለሥልጣናትም የተገኙበት ነበር።

መዘክርም በበኲሉ ከጣልያን ወረራ ጋራ በተያያዘ ለመከራ፣ ለሥቃይ፣ ለሞት እንዲኹም ለንብረት ውድመት የተዳረጉ ቤተሰቦችን በሙሉ የሚዘክር መታሰቢያ የማኖር ዕቅድ አለው። በአዚናራ ቋሚ መታሰቢያ እንዲኖር የሚደረገው ጥረትም የዚሁ ዐላማ አካል ነው። የሳሳሪውን ጉዟችንን የሚያሳይ አጭር ቪዲዮ በዚህ ማስፈንጠሪያ ይገኛል።

ፅሑፎች

ቀኛዝማች ፀምሩ 1960
ቀኛዝማች ፀምሩ 1960

ቀኛዝማች ፀምሩና ቤተሰባቸው

ቀኛዝማች ፀምሩ ገብረ ሥላሴ ከእናታቸው ከክብርት ወይዘሮ እሴተ እና ከአባታቸው ከክቡር ፀሓፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ በ1887 ደብረ ብርሃን ከተማ ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም በባሕላዊው የቄስ ትምህርት ገብተው ከተማሩ በኋላ፤ ከወይዘሮ ሠናይት ወልደ ገብርኤል ጋራ ትዳር መሥርተው ዐሥራ ስድስት ልጆችን አፍርተው አሳድገዋል።

ይቀጥላል...
አቶ መኮንን ወልደዮሐንስ
አቶ መኮንን ወልደዮሐንስ

አቶ መኮንን ወልደ ዮሐንስ እና ሥራዎቻቸው

አቶ መኮንን ወልደ ዮሐንስ ከእናታቸው ከወይዘሮ ወደርየለሽ ወልደ ገብርኤል እና ከአባታቸው ከአቶ ወልደ ዮሐንስ ናደው በሐምሌ 13 ቀን፣ 1897 በዐዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። እናታቸው ወይዘሮ ወደርየለሽ የመንዝ ተወላጅ ሲኾኑ፣ ዐዲስ አበባ ከተማ አነስተኛ ሱቅ ነበራቸው። አባታቸው አቶ ወልደ ዮሐንስ ናደው ደግሞ ኮርቻ፣ አፎት እና የተለያዩ የቆዳ ምርቶችን በመሥራት የሚታወቁ የቡልጋ ሰው ነበሩ።

ይቀጥላል...
መርካቶ የሚገኘው አሜሪካን ግቢ።
መርካቶ የሚገኘው አሜሪካን ግቢ።

አሜሪካን ግቢ

በ1910 አጋማሽ፣ በዘመነ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ፣ መርካቶ አካባቢ አንድ የድንጋይ ሕንጻ ተገነባ። ሕንጻው የተገነባው በወቅቱ የጦር ሚኒስትር ለነበሩት ለፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ መኖርያ እንዲኾን ታስቦ ነው። የጦር ሚኒስትሩ ወደዚኽ መኖርያ ቤት ከመዘዋወራቸው በፊት አሁን የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን የቆመበት ስፍራ ላይ የተሠራ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበር። የእርሳቸው አጃቢዎችም እዚያው አካባቢ ይኖሩ ስለነበረ መርካቶ ዙሪያ ሰፊ መሬትና ንብረት ነበራቸው። በርግጥ ያ በድንጋይ የተሠራና ግርማ ሞገስ ያለው ሕንጻ መኖሪያ ቤታቸው ብቻ ሳይኾን፤ ችሎት ማስቻያቸውም ነው።

ይቀጥላል...

ሰሞነኛ ሁነቶች

የድርጅታችን መጠሪያ ስም

"From Oblivion to Memory  (F.O.M.)" ድርጅታችንን ወክሎ በመጠሪያነት የሚያገለግል የእንግሊዘኛ ስም እንደኾነ ይታወቃል። ከእንግሊዘኛው በተጨማሪ ድርጅታችን የዐማርኛ እና የጣልያንኛ ስም ያስፈልገው ስለነበረ፤ በዐማርኛ "መዘክር" በጣልያንኛ ደግሞ "Dall’Oblio alla Memoria" የድርጅታችን መጠሪያ ስም እንዲኾን ተወስኗል። ስያሜው ይኽ የሆነበት ምክንያት  ለመጥራትም ኾነ ለማስታወስ የሚመች፣ ብሎም ዐላማውን በተወሰነ ደረጃ  ሊገልፅ የሚችል ስለኾነ ነው። ከታች የምትመለከቱት ዐርማ የድርጅታችንን የዐማርኛ እና የእንግሊዘኛ ስያሜ አካትቶ የያዘ ነው።

የጠቅላላ ስብሰባ ጥሪ

ቅዳሜ መስከረም 23 ቀን 2019 (October 3, 2026) በአዲስ አበባ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰዓት (1:00 p.m. Eastern time) በተዘጋጀው የአባላት፣ ደጋፊዎችና ወዳጆች ስብሰባ ላይ እንድትገኙ መዘክር በአክብሮት ይጋብዛችኋል። ይህን ጥሪ ለሌሎችም በማጋራት ተባብራችሁን ያልሰሙ ወገኖችንም ጋብዙልን። እናመሰግናለን።

አስተዋጽዖ አበርካቾቻችን

በዚህ በየሦስት ወሩ የሚወጣ ዝግጅታችን ሁለተኛው ዕትም ላይ ለተሳተፉትና ስማቸው ከዚህ በታች ለተጠቀሰው ሰዎች ምስጋና እናቀርባለን።

መረጃ ለማሰባሰብ፦

ኤደን ደበበ እና ካሌብ ደበበ።

ለምርምር፣ ለጽሑፍ እና ለዕርማት፦

ተስፋዬ አድኃኖም፣ አስቴር አንቶሒን፣ ጌታብቻ መኮንን፣ ላቀች መኮንን፣ ኒቆዲሞስ መኮንን፣ መቅደስ መስፍን፣ ዋሲ ተስፋ፣ ሊዲያ ተስፋዬ እና ያድዋ የወንድወሰን።ለትርጉም፦ ደብሪቱ መርዕድ ካምፖሬያሊ፣ ጋብሪኤላ ጌርማንዲ፣ ኃይሌ ከበደ፣ አንጄሊካ ፔሳሪኒ እና መቅደስ መስፍን።

ለትርጉም ሥራ:-

ደብሪቱ መርዕድ ካምፖሬአሊ፣ ጋብሪዬላ ጌርማንዲ ፣ ኃይሌ ከበደ፣ መቅደስ መስፍን እና አንጄሊካ ፔሳሪኒ

ለህትመት፦

ይጥና ፍርድይወቅ እና ኤልፊ ጌታቸው ኑቬሎን።