FROM OBLIVION TO MEMORYThe FOM NewsletterCommemorating Ethiopian prisoners of the Italo-Ethiopian Warቅጽ 1 · ቁጥር 2መስከረም/ጥቅምትfromobliviontomemory.org

ቀኛዝማች ፀምሩና ቤተሰባቸው

ቀኛዝማች ፀምሩ ገብረሥላሴ

ቀኛዝማች ፀምሩ 1960
ቀኛዝማች ፀምሩ 1960

ቀኛዝማች ፀምሩ ገብረ ሥላሴ ከእናታቸው ክብርት ወይዘሮ እሴተ እና ከአባታቸው ከክቡር ፀሓፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ በ1887 ደብረ ብርሃን ከተማ ተወለዱ። ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰም በባሕላዊው የቄስ ትምህርት ገብተው ከተማሩ በኋላ፤ ከወይዘሮ ሠናይት ወልደ ገብርኤል ጋራ ትዳር መሥርተው ዐሥራ ስድስት ልጆችን አፍርተው አሳድገዋል።

ቀኛዝማች ፀምሩ 1934
ቀኛዝማች ፀምሩ 1934

ቀኛዝማች ፀምሩ ሀገራቸውን በተለያየ የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች በብቃት አገልግለው ለአገልግሎታቸው የኒሻን ሽልማቶችን የተቀበሉ ሰው ናቸው። በተለያዩ ጊዜያት በጽሕፈት ሚኒስቴር እና በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ዋና አስተዳዳሪ በመኾን ሠርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም በ1913 በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን በሐረርና በወላይታ ነጋድራስ ኾነው አገልግለዋል።

አስከፊው የአዚናራ ደሴት የእስር ዘመናቸው አብቅቶ ዐዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላም የሐምሌ 16 ኮሚቴ [1] አባል በመኾንም የሠሩ ሲኾን፤ ከዚያም ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ የሕዝብ ምክር ቤት አባል ኾነው ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን አገልግለዋል። ቀኛዝማች ፀምሩ በ77 ዓመት ዕድሜያቸው ከዚህ ዓለም ድካም አርፈው በእንጦጦ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ ቀብራቸው ተፈጽሟል።

ሻለቃ ጌታብቻ ፀምሩ

ጌታብቻ ፀምሩ
ጌታብቻ ፀምሩ

ጌታ ብቻ ፀምሩ የቀኛዝማች ፀምሩ የበኲር ልጅ ሲኾኑ አዚናራ ከመታሰራቸው በፊት የሻለቃነት ማዕረግ የተቀበሉ ሰው ናቸው። በታሰሩ ጊዜ ገና ትዳር አልመሠረቱም ነበር ። ጌታ ብቻ አዚናራ በእስር ላይ እያሉ በሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ሞታቸው ቤተ ሰቡን ለከፍተኛ ሀዘን የዳረገ ሲኾን ሀዘኑን ያከፋው ደግሞ ትዳር ሳይመሠርቱና ዘራቸውን ሳይተኩ በሰው ሀገር መሞታቸው ነው። የሻለቃ ጌታ ብቻ ፀምሩን መሞት ቤተ ሰቡ ያወቀው ወንድማቸው ጥጋሻው በእስር ላይ ኾነው ለወንድማቸው ደበበ ፀምሩ ጽፈው የላኩት ደብዳቤ ላይ የጌታ ብቻ ፊርማ ባለመኖሩ ነበር።

አቶ ደበበ የወንድማቸውን ሞት በግምት እንደደረሱበት ለጥጋሻው የገለፁበት ደብዳቤ
አቶ ደበበ የወንድማቸውን ሞት በግምት እንደደረሱበት ለጥጋሻው የገለፁበት ደብዳቤ

ለዚህ ፅሑፍ ዝግጅት ሲባል በተደረገው ምርምር አዚናራ በእሥር አብረዋቸው የቆዩት ቀኛዝማች ደህኔ ወልደ ማርያም ማስታወሻ ላይ የሚከተለው ቃል ሰፍሯል። "የካቲት 1 ቀን ጌታ ብቻ የሚባል የቀኛዝማች ጸምሩ ገብረ ሥላሴ ልጅ ታሞ ሰንብቶ ስላረፈ የወይዘሮ ሮማን ወርቅ ልጅ ከተቀበረበት ቦታ እዚሁ አዚናራ ተቀበረ። አባ በርሳሊና ባመጡልን ዳዊት ሰባት ቀን ጸሎተ ፍትሐት ተደረገለት።" በ2017 አዚናራ ላይ በተደረገው ጉብኝት “ካምፖ ፋሮ” መካነ መቃብር ያረፉት ኢትዮጵያውያን ላረፉበት ቦታ ምንም ምልክት እንዳልተደረገላቸው አስተውለናል። የነበሩት ጥቂት ምልክቶች በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ጊዜ ለሞቱ እስረኞች ብቻ የተደረጉ ከመኾናቸው በላይ የመቃብር ቦታው መፈራረስ ላይ ያለና ምንም እንክብካቤ ያልተደረገለት ነው።

ጥጋሻው ፀምሩ

ኮሎኔል ጥጋሻው ፀምሩ
ኮሎኔል ጥጋሻው ፀምሩ

የቀኛዝማች ፀምሩ ኹለተኛ ልጅ የኾኑት ጥጋሻው ፀምሩ ሐምሌ 6 ቀን 1895 በዐዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ። ከወይዘሮ ሮማን መኮንን ጋር በትዳር በኖሩበት ዘመን አራት ልጆችን አፍርተው አሳድገዋል። አዚናራ በእስር ከነበሩበት ተመልሰው የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎችን በመቀላቀል የኮሎኔልነት ማዕረግ ደርሰዋል። በኋላም የሚሊታሪ ዳኛ ኾነው አገልግለዋል። ኮሎኔል ጥጋሻው በ1960ዎቹ ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

እስር በአዚናራ ደሴት

ቀኛዝማች ፀምሩ በአዚናራ 1938
ቀኛዝማች ፀምሩ በአዚናራ 1938

ከየካቲት 12 ጭፍጨፋ ጋር ተያይዞ የጣልያን መንግሥት ቀኛዝማች ፀምሩና ኹለት ልጆቻቸውን ጨምሮ ማኅበረ ሰቡ ላይ ተጽዕኖ የመፍጠር ዐቅም አላቸው ያላቸውን፣ ሀገራቸውን ከጠላት ወረራ ይከላከላሉ ብሎ የጠረጠራቸውን፣ ትምህርት ወይ ሥልጣን ያላቸውን እና መሰል ሰዎችን በማሰር በመርከብ ወደ አዚናራ ደሴት የወሰዳቸው ሲኾን ከኹለት ዓመት እስር በኋላ ቀኛዝማች ፀምሩ ከአንድ ልጃቸው ጋር ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ በቅተዋል።

በዚኽ ወቅት ስለነበረው ኹኔታ ያለው ጥቂት መረጃ የተገኘው ቀኛዝማች ፀምሩ ከባለቤታቸው ወይዘሮ ሠናይት ወልደ ገብርኤል እና ልጃቸው ጥጋሻው ፀምሩ ከወንድም እኅቶቻቸው ጋር ከተጻጻፏቸው ጥቂት ደብዳቤዎች ብቻ ነው። አንዳንድ እስረኞች ኢትዮጵያ ለሚገኙት ቤተ ሰቦቻቸው ፎቶግራፍ መላካቸውን፣እሱንም ተከትሎ የእስረኞቹ ዘመዶች ፎቶግራፎቻቸውን ለማየት እና ስለእነርሱ ዜና ለመስማት እጅጉን መናፈቃቸውን እንዲኹም ካለፈቃዳቸው ከቤተ ሰቦቻቸው ጋራ በመለያየታቸው መጎዳታቸውን ከተላኳኳቸው ደብዳቤዎች ለማወቅ ተችሏል።

የመዛግብት ጥናትና ያልተመለሱ ጥያቄዎች

ቀኛዝማች ፀምሩ
ቀኛዝማች ፀምሩ

የቀኛዝማች ፀምሩን እና ልጆቻቸውን እስር በሚመለከት እስካሁን የተገኙት መረጃዎች ቁንጽል በመኾናቸው፤ ስለእነርሱ መያዝ፣ የእስር ቆይታና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ቤተ ሰቦቻቸው የሚያውቁት ነገር በጣም ጥቂት ነው። በተለይ ስለ ጌታ ብቻ አሟሟትና ቀብር ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ምናልባትም በጣልያን ኾነ በኢትዮጵያ መዛግብት ውስጥ የሚገኝ ዐዲስ መረጃ ካለ ነገሩን ሊቀየረው ይችል ይኾናል ።

የቤተሰብ ገጠመኝ

ቀኛዝማች ፀምሩና ባለቤታቸው እንጦጦ አካባቢ ቤተሰባቸውን ይዘው ይኖሩ የነበረበትን ትልቅ ባለ ሁለት ፎቅ ቤት አንድ የወራሪው የኢጣልያ ሹም ቀምቷቸው ከነቤተሰቡ ይኖርበት ነበር። በዚህን ጊዜ የኢጣልያዊው አንድ ወንድ ልጅና የሳቸው አንድ ወንድ ልጅ ጓደኝነት መሥርተው በልጅ የዋህነት ጊዜአቸውን አብረው ያሳልፉ ነበር። ከወረራው በኋላ ኢጣልያዊው ቤተሰቡን ይዞ ወደ አገሩ ተመለሰ። ነፍስ ካወቁ በኋላ ኒኒና አልማ የሚባሉ ሁለት የኢጣልያዊው ልጆች ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት መጥተው በልጅነት የኖሩበትን ቤት ሊያዩ መጥተው ነበር።

አቶ ደበበ ከልጅነት ባልንጀራቸው እና አንድ ማንነታቸው ያልታወቀ እንግዳ ጋር
አቶ ደበበ ከልጅነት ባልንጀራቸው እና አንድ ማንነታቸው ያልታወቀ እንግዳ ጋር

እዚህ ፎቶ ላይ የሚታዩት የጥጋሻውና የጌታ ብቻ ታናሽ ወንድም የኾኑት አቶ ደበበ ፀምሩ ከእነዚኽ የልጅነት ጓደኞቻቸው ከነበሩ የጣልያን ሹም ልጆች ጋር ተገናኝተው ሳለ ነው። በዚኽ አጋጣሚ አቶ ደበበ በአንድ የባህል ምግብ ቤት ለእንግዶቹ ግሩም መስተንግዶ አድርገውላቸዋል።

__________

1 የሐምሌ 16 ኮሚቴ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የልደት በዓል ኮሚቴ ነው።