FROM OBLIVION TO MEMORYThe FOM NewsletterCommemorating Ethiopian prisoners of the Italo-Ethiopian Warቅጽ 1 · ቁጥር 2መስከረም/ጥቅምትfromobliviontomemory.org

አቶ መኮንን ወልደ ዮሐንስ እና ሥራዎቻቸው

አቶ መኮንን ወልደዮሐንስ
አቶ መኮንን ወልደዮሐንስ

አቶ መኮንን ወልደ ዮሐንስ ከእናታቸው ከወይዘሮ ወደርየለሽ ወልደ ገብርኤል እና ከአባታቸው ከአቶ ወልደ ዮሐንስ ናደው በሐምሌ 13 ቀን፣ 1897 በዐዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። እናታቸው ወይዘሮ ወደርየለሽ የመንዝ ተወላጅ ሲኾኑ፣ ዐዲስ አበባ ከተማ አነስተኛ ሱቅ ነበራቸው። አባታቸው አቶ ወልደ ዮሐንስ ናደው ደግሞ ኮርቻ፣ አፎት እና የተለያዩ የቆዳ ምርቶችን በመሥራት የሚታወቁ የቡልጋ ሰው ነበሩ።

አቶ መኮንን ወልደ ዮሐንስ ቀበና አካባቢ በሚገኘው የወላጆቻቸው ቤት ከሦስት ወንድሞቻቸው እና ከአንድ እኅታቸው ጋር የኖሩ ሲኾን፤ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ መጀመሪያ በቄስ ትምህርት ቤት በኋላም ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው በጊዜው በፈረንሳይኛ የሚሰጠውን የሒሳብ እና የሣይንስ ዘመናዊ ትምህርት በጥሩ ኹኔታ ተከታትለዋል። አቶ መኮንን ትጉህና ሥራ ወዳድ በመሆናቸውም በግል የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ትልቅ ስኬት አሳይተዋል።

በወረራው ወቅት

ፋሺስት ጣልያን ሀገራችን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት፤ አቶ መኮንን ወንድማቸው ጸሓፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስን ተከትለው በመዝመት መጋቢት 22 ቀን 1928 በማይጨው ጦርነት ቆስለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አርበኞች ተጋድሎ ወደ ሽምቅ ውጊያ በተዘዋወረበትም ወቅትም እርሳቸው እና ቤተ ሰባቸው ከባድ ዋጋ ለሀገራቸው ከፍለዋል። በዚህ ጊዜ አባታቸው አርበኞችን ረድተዋል በሚል ሰበብ ሲገደሉ፤ ታላቅ ወንድማቸው ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱን ተከትለው ከሀገር ወጥተዋል።

ታዲያ በዚያ አስቸጋሪ ወቅት ወጣቱ አቶ መኮንን የቤተ ሰባቸው ኀላፊ በመኾን ከዕድሜያቸው በላይ የኾነ ከባድ ሸክም ለመቀበል ተገደዋል። ከቤተ ሰብ ኀላፊነታቸው በተጨማሪም የውስጥ አርበኛ በመኾን ሀገራዊ ግዴታቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል፡፡

አቶ መኮንን ወልደ ዮሐንስ (በስተቀኝ) ከወንድማቸው ከፀሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ጋር በጦር ሜዳ 1936
አቶ መኮንን ወልደ ዮሐንስ (በስተቀኝ) ከወንድማቸው ከፀሐፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ጋር በጦር ሜዳ 1936

አቶ መኮንን፤ የካቲት 12 ቀን 1929 ግራዚያኒ ላይ በተደረገው የግድያ ሙከራ ሰበብ ታስረው ወደ ጣልያን ሀገር የተወሰዱ ሲኾን፤ መጀመሪያ አዚናራ ከዚያም ሜርኮሊያኖ ካምፕ እስረኛ ኾነው ቆይተዋል። አቶ መኮንን ከእስር ተለቅቀው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የመጡበትን ትክክለኛ ቀን የሚናገር ማስረጃ ባይገኝም፤ ከድል በፊት በ1931 አብዛኞቹ እስረኞች በተለቀቁበት ወቅት እርሳቸውም ተለቅቀዋል ተብሎ ይገመታል፡፡

አቶ መኮንን ለቤተ ሰቦቻቸው ተናግረውት እንደነበረው ከኾነ የአዚናራ የእስር ቆይታቸው ለእርሳቸውና አብረዋቸው ለነበሩት ኢትዮጵያውያን እጅግ አስከፊ ነበር፡፡ በዚያ አስከፊ ኹኔታ ውስጥ ኾነው እውቀታቸውን በማሻሻል ጣልያንኛ ቋንቋን ተምረዋል። በተግባረ ዕድ ትምህርት በመሠማራትም የልብስ ስፌት እና የአናጢነት ሙያ ተምረዋል፡፡ በወቅቱ ፋሽስት ጣልያን የአቶ መኮንንን ሙያ በአግባቡ ተጠቅሞበታል፡፡ በልብስ ስፌት ሙያቸው፤ በእርሻ እና በቤት ውስጥ ሥራ አገልግሎት ላይ ለዋሉ እስረኞች የሚኾን የደንብ ልብስ እንዲሰፉ፤ በአናጢነት ሙያቸው ደግሞ ለእስር ቤቱ አገልግሎት የሚውል ወንበር፣ ጠረጴዛ እና የመሳሰሉትን እንዲሠሩ ያደርጋቸው ነበር።

አቶ መኮንን ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጋር በነበራቸው አለመግባባት ከመንግሥት ሥራ ሲገለሉም፣ የልብስ ስፌት ሙያቸውን በመጠቀም የገዛ ልጆቻቸውን ልብስ በመስፋት ያለብሱ ነበር። የቅርብ ቤተ ሰባቸውንና ነፃነታቸውን ባጡ ሰዐት እንኳን ራሳቸውን ለማሻሻል ወደ ኋላ የማይሉ ብርቱ ሰው ነበሩ።

የሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ

አቶ መኮንን ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከታላቅ ወንድማቸው ጋር በመኾን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ዐዲስ መንግሥት ለማቋቋም የራሳቸውን አስተዋጽኦ በማድረግ በሙያቸው በቅንነት እና በትጋት ያገለገሉ ሰው ናቸው።

የጦርነቱ ካሣ አፈጻጸም ኀላፊነት ተሰጥቷቸው ከማገልገላቸውም በተጨማሪ፤ አቶ መኮንን ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነውን የአባ ሳሙኤል ሃይድሮ ኤሌክትሪክ ኀይል ማመንጫ ተቋም እድሳት አካሂደው፤ በተጨማሪነትም ዐዳዲስ ተርባይኖች እንዲገጠሙ በማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይል ስርጭት እንዲስፋፋ አድርገዋል። ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ባለሥልጣን ሲቋቋም በሥራ አስኪያጅነት በመምራት፤ መኻል አዲስ አበባ ፒያሳ ላይ ለድርጅቱ ግዙፍ ሕንጻ አስገንብተዋል፡፡ ይኽ ታሪካዊ ሕንጻ አኹንም ድረስ ለገነቡት ተቋም ሕያው ምስከር ኾኖ ይታያል።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት (በስተቀኝ) እና አቶ መኮንን በስተግራ የአባ ሳሙኤል ተርባይኖች ምረቃ ላይ 1935 ገደማ
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት (በስተቀኝ) እና አቶ መኮንን በስተግራ የአባ ሳሙኤል ተርባይኖች ምረቃ ላይ 1935 ገደማ

አቶ መኮንን ለኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሕዝብ ማመላለሻ አገልግሎት የኾነውን አንበሳ አውቶቡስንም ለመመሥረት ተግተው ከሠሩት ወገኖች መኻል አንዱ በመኾን፤ ሕዝብን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በትራንስፖርት በማጓጓዝ እና ከተማን በማዘመን ሂደት ላይ የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ ታላቅ ሰው ናቸው።

አቶ መኮንን፤ ከዘመን ተጋሪዎቻቸው ጋራ በመኾን ሀገራቸውን ከጦርነት እና ከወረራ እንድታገግም ለማድረግና ለመለወጥ ትልቅ ራዕይ ነበራቸው፡፡ ከ1940ዎቹ መጨረሻ እስከ 50ዎቹ መጀመሪያ የሀገራቸውን ግንባታ በትጋት ሲከታተሉና ሲያካሄዱ ከቆዩ በኋላ፤ በጊዜው በተፈጠሩ አንዳንድ የፖሊቲካ ውጥረቶች መካከል እክል ገጥሟቸው፤ እርሳቸውና ተፅዕኖ ፈጣሪው ወንድማቸው ጸሓፌ ትእዛዝ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ ላይ ሹም ሽር ተካሄዷል። በዚህም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለዐሥራ አምስት ዓመታት በግዞት ታስረው ኖረዋል።

አቶ መኮንን (ወረቀት ይዘው የሚያነብቡት) የመጀመሪያው ሥራ አስኪያጅ ሆነው ባገለገሉበት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ፅሕፈት ቤት ሆነው በ1940 ገደማ
አቶ መኮንን (ወረቀት ይዘው የሚያነብቡት) የመጀመሪያው ሥራ አስኪያጅ ሆነው ባገለገሉበት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ፅሕፈት ቤት ሆነው በ1940 ገደማ

የግል ሕይወት

አቶ መኮንን ወይዘሮ ቆንጂት ዘውገን አግብተው ዐሥር ልጆችን ወልደው አሳድገዋል። በስተርጅና ዘመናቸውም ከሃያ የልጅ ልጆቻቸው ጋር ለሚያሳልፉት ጊዜ እጅግ ትልቅ ዋጋ ይሰጡ ነበር። የቤታቸውም አስተዳደር ልክ እንደ ሥራቸው፤ ትጋት፣ ጽናት እና ፍቅር፣ ይንፀባረቅበት ነበር።

አቶ መኮንን ከመንግሥት ሥራ ከተገለሉ በኋላ እጃቸውን አጣምረው የተቀመጡ ሰው አልነበሩም። ዐዲስ አበባ ውስጥ የከብት እርባታ ከመጀመራቸውም በላይ ከአዚናራ እስር ቤት በቀሰሙት ሙያ ዕድሜ ልካቸውን የተዋጣላቸው ግንበኛ እና አናጢ በመኾን ቤታቸውን እና አካባቢያቸውን በአግባቡ የተንከባከቡ ሰው ነበሩ።

አቶ መኮንን ወልደ ዮሐንስ በ85 ዓመት ዕድሜያቸው ታኅሣስ 20 ቀን 1983 ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተው ሥርዐተ ቀብራቸው በቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።

ቅርስ

አቶ መኮንን ሀብተወልድ፤ ከቄስ ትምህርት ቤት እስከ ጦር ሜዳ፣ ከባዕድ ሀገር የእስር ቤት ቆይታና የብቸኝነት ጊዜ እስከ ታላላቅ የመንግሥት ሥራ ኀላፊ በመኾን ሀገር በማቅናት፤ ከዚያም ሲቀጥል በጡረታ ዕድሜያቸው ቤት እና አካባቢን በመገንባት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ ብርቱ ሰው ናቸው። በሥራ ዘመናቸውም ያተረፉት እውቅና ከትህትናቸው እና ከትጋታቸው የመጣ እንጂ በሥልጣንና ማዕረጋቸው ያገኙት አልነበረም። ለሀገራቸው ኢትዮጵያ እንዲኹም ለቤተ ሰባቸው ባደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ ከአባ ሳሙኤል ተርባይኖች ጀምሮ እስከ አንበሳ አውቶብስ ድርጅት፤ ከግዙፉና ታሪካዊው የመብራት ኃይል ሕንጻ እስከ መኖርያ ቤታቸውና አከባቢያቸው ድረስ አሻራቸውን ያስቀመጡ ትውልድ የሚዘክራቸው ታላቅ ሰው ናቸው።

አቶ መኮንን ወልደዮሐንስ 1970
አቶ መኮንን ወልደዮሐንስ 1970