The FOM Newsletter masthead

ከዝግጅት ክፍላችን

እንኳን ወደ መጀመሪያ እትማችን በደህና መጣችሁ!

እኛ በፋሺስት ኢጣልያ ጨካኝ የወረራ ዘመን ከአገራቸው ተግዘው በኢጣልያና በሌሎች አገሮች ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ተወላጆች ስንሆን የእስረኞቹ ታሪክ ደብዝዞ እየጠፋ መሆኑን በመገንዘብና የደረሰባቸውን እንግልትና የከፈሉትን መስዋዕትነት መዘከር ግዴታ መሆኑን በመረዳት በመተባበር ማሕበር አቋቁመናል።

ይህም ዕድል የተፈጠረው የኛው ዘመዶች ታስረው የነበረበትን አዚናራ ደሴትን ለመጎብኘት በነሐሴ 2017 የተወሰንን የቤተሰብ አባላት ወደዚያው ባቀናንበት ወቅት ነበር። እስር ቤቱን ስንጎበኝ፣ ካላ ሬያሌ በሚገኘው ሆስፒታል ሕንፃ ውስጥ ግርግዳው ላይ የአንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት፣ ከአንድ ትንሽ ወንድና አንዲት ትንሽ ሴት ልጅ ጋር የተነሳችው ትልቅ ፎቶግራፍ ተሰቅሎ አየን። ከዚያን ዘመን እስረኞች መካከል ዛሬ በሕይወት ያሉት ያቺ በፎቶግራፉ ላይ የምትገኘው ትንሿ ልጅ፣ የዛሬይቱ የ94 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ብቻ ናቸው።

ይህ ከብዙ አሥርት ዓመታት በኋላ የተደረገ ጉዞ ይህን ታሪክ ሰብስቦ ማቆየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እጅግ አመላካች የሆነ አጋጣሚ ነበር። ለዚህም ነው ወደየመጣንበት ከተመለስን በኋላ ድርጅት አቋቁመን ይህን ዓላማ ለማሳካት ጥናት ማካሄድ፣ ወገን ማነቃቃትና መደራጀት የጀመርነው። ይህም የመጀመሪያው እትማችን ለዚህ ሁሉ ዘመናት ድምፃቸው ያልተሰማላቸው ወገኖቻችንን ታሪክ ለመንገር ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል።

እኛም በየግዜው ከሌሎች እስረኞች ተወላጆች ጋር በያሉበት ዘላቂ የሆነ ግንኙነት ለመመሥረት እንጥራለን። ይህ ታሪክ ከኛ ጋር የሚያስተሳስራችሁ፣ እንዲሁም ታሪኩና ዓላማው የሚማርካችሁ ሁሉ አብራችሁን እንድትጓዙም እንጋብዛለን። በሕይወት ጉዞ ውስጥ የዚህን ታሪክ ትውስታን ለማጎልበት፣ በማንኛውም ረገድ የምታደርጉት ትብብር ለታለመው እቅድ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።

አብረን ሆነን ያለፈውን በማስታወስ ለወደፊቱ ትውልድ የሚሆን ቅርስ እንገነባለን። በዚህ በመጀመሪያው ቅፅ በዚያን ዘመን እስረኛ የነበሩ ሁለት ሰዎች ታሪክ ቀርቧል፣ እንዲሁም አንድ ታሪካዊ ክስተት ተዘግቦ ለንባብ ቀርቧል። በቀጣይ እትሞቻችንም፣ የተለያዩ ሰዎች የሕይወት ታሪክ መዘከሩን እንቀጥላለን።

ሰሞነኛ ሁነቶች

የ AAIS ስብሰባ

በመጭው የኢጣልያ ጥናት በአሜሪካ ማሕበር ስብሰባ ላይ ተገኝተን ድርጅታችንን ለማስተዋወቅ ባገኘነው ዕድል መሠረት ይህንን ጥናታዊ ስብሰባ ለመካፈል ዝግጅት ላይ እንገናኛለን። ስብሰባው የሚካሄደው ሳሳሪ ሳርዴኛ፣ ኢጣልያ ከሰኔ 3–5 2018 ድረስ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ የፓነል ውይይት የሚሳተፉ ተወካዮች ይኖሩናል።

የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት

ከዚህ ቀደም ተዘጋጅቶ ከነበረው በራሪ በተሻለ መልኩ አስረጂ የሆነ፣ ጥረታችንን ሁሉ በደንብ የሚገልፅና ድርጅቱን በደንብ የሚያስተዋውቅ፣ በፒዲኤፍ ማውረድ የሚቻል እሱን የሚተካ ሰነድ አዘጋጅተን በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን። እንዳለቀም ከድረ-ገፁ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።

ነሐሴ 2018 ሲመጣ አዚናራ ከሄድን ዓመት ይሞላናል። ለዚህም መታሰቢያ በሚሆን መልኩ ዓመት እስኪሞላን ድረስ $20,000 ለመሰብሰብ እንድንረባረብ ባቀረብነው ጥሪ መሠረት እስከ አሁን የተሰበሰበውና ቃል የተገባው ድምር $6,000 ነው።

ዋናው ዓላማችን አዚናራ ደሴት ላይ እዚያ ታስረው የነበሩ ወገኖቻችንን የምናስብበትና የምንዘክርበት ሚዩዚየም ማቆም ነው። አንዳንዶቹ ካምፖ ፋሮ መቃብር ቦታ ላይ ምልክት እንኳ በሌለው መቃብር አርፈዋል። ይህን ለማድረግ በተቻላችሁ መጠን ዓላማችንን እንደምትደግፉ ተስፋ አለን። እባካችሁ የገንዘብ ድጋፍም አድርጉልን። ማንኛውም የገንዘብ ድጋፍ ደረሰኝ የሚሰጥበትና ከግብር ነፃ የሚሆን ነው።

አዲሱ ድረ-ገፃችን! FOM 2.0

አዲሱ FOM 2.0 ብለን የምንጠራው ድረ-ገፃችን መከፈቱን ስንገልፅላችሁ በደስታ ነው። ፒዬር ሀብቴ፣ ኤልፊና ይጥና እጅግ ደክመው ይህንን የተለየ ዲጂታል ጥራትና አቅም ያለውን ድረ-ገፅ በብዙ ወራት ልፋት እዚህ ስላደረሱልን በጣም እናመሰግናቸዋለን። ይህ አዲስ ድረ-ገፅ መዛግብት በውስጡ ለመያዝ ልዩ አቅም እንዲኖረው ሆኖ የተሠራ ነው። ወገኖቻችን ከእስር በፊት፣ ታስረው ሳለና ከተፈቱም በኋላ በአግባቡ ለመሰነድ ስለሚመቸን፣ ከዓላማችን ጋር እጅጉን የተጣጣመ ነው ብለን እናምናለን።

እባክዎ አዲሱን ድረ-ገፅ www.fromobliviontomemory.org ይጎብኙ። እግረ-መንገድዎን አዲስ የነደፍነውን የመገናኛ መንገድም ይፈትሹ!

የምናወጣቸው መረጃዎች የሚያስደስቱዎ ከሆኑ እባክዎ ድጋፍዎን ይስጡን፦

አስተዋጽዖ አበርካቾቻችን

ይህ በየሦስት ወሩ የሚወጣ ዝግጅት ሲሆን የዛሬው የመጀመሪያው እትም ላይ ለተሳተፉትና ስማቸው ከዚህ በታች ለተጠቀሰው ምስጋናችን የላቀ ነው፦
ለምርምር፣ ለጽሑፍ እና ለዕርማት፦ ጎሕዓለም አሰፋ፣ እጅጋየሁ ደምሴ፣ ይጥና ፍርድይወቅ፣ ብርሃኔ ግርማቸው፣ መቅደስ መስፍን፣ ዋሲ ተስፋ፣ ሊዲያ ተስፋዬ፤ ያድዋ የወንድወሰን እና ዳግማዊ ይመር።
ለትርጉም፦ ደብሪቱ መርዕድ ካምፖሬያሊ፣ ጋብሪኤላ ጌርማንዲ፣ ኃይሌ ከበደ፣ ቆንጂት ሥዩም።
ለፎቶዎችና ምስሎች፦ ኤልፊ ጌታቸው ኑቬሎን፣ እያሱ ቤትዎስ፣ አሉላ ፓንክኸርስት።